በትግራይ ክልል በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሀ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ እና የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ህብረተሰቡ ተሳትፈዋል።
አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የትግራይ ክልል በተፋሰስ ልማትና ችግኝ ተከላ የታወቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሁን የተገኘውን ሰለም በማጽናት የበለጠ የልማት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ሰላሙን ለማጽናት የፌዴራል መንግስት ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ ሰላም ሰፍኖ ወደዚህ አይነት የልማት ተግባር መመለስ መቻሉ መልካም እንደሆነ ተናግረው፤ የተገኘውን ሰላም ለማጽናት ጠንክረው እንደሚሰሩ ማብራራታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።