Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብሯን አሳካች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን በላይ ችግኝ የመትከል መርሐ ግብሯን ማሳካቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከችግኝ ተከላ ሁነቶች መከታተያ ክፍል በሰጡት መግለጫ÷ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የአንድ ጀንበር ከ566 ሚሊየን በላይ ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ዜጎች በንቃት መሳተፋቸውን አንስተዋል፡፡

በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ አካባቢ ከማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ከ566 ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ነው የተናገሩት፡፡

አቀድን፤ ተባበርን፤ አሳካን፤ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) መርሐ ግብሩ እንዲሳካ ልጆቻቸውን አቅፈው ችግኝ ለተከሉ እናቶች፣ ሕጻናትና ተማሪዎች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የእንኳን ደስአላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ እንዲሁም ለመላው ዓለም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥና እጅግ የሚያኮራ ተግባር ፈጽመናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የዓየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ ስጋት መሆኑ ታምኖ በጉዳዩ ላይ ንግግር ከተጀመረ መቆየቱን አንስተው÷ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ባከናወነችው ልክ የተጀመሩ ስራዎች ጠንካራ አለመሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ዛሬ በተካሄደው በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን  ችግኝ የመትከል መርሐ ግብርም 566 ሚሊየን 971 ሺህ 600  ችግኝ በ302 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መተከሉን ጠቁመዋል፡፡

በሪፖርቱ የቀረበው ችግኝ የተተከለበት ቦታ የሚታወቅ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን መስፈርት ያሟላ ብቻ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

ዛሬ የሰራነውን አስደናቂ ገድል በድህነት እንዲሁም ሰላም እና ሌሎች ችግሮች ላይ ለመድገም መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ለዚህም ከጥላቻ፣ ጸብ፣ መገፋፋት እና ኩርፊያ መውጣት አለብን ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

“መሰዳደብ፣ መዋጋት ፣ መገፋፋት ይብቃን፤ ወደ ሰላም መጥተን ተባብረን ኢትዮጵያን ለመቀየር እንስራ” ሲሉም ለፖለቲከኞች፣ ማኅበራዊ አንቂዎችና በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ አካላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.