Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል በኩል አርአያነት ያለው ተጨባጭ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን አምባሳደሮች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል በኩል አርአያነት ያለው ተጨባጭ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ የተሳተፉ የኢራንና የፈረንሳይ አምባሳደሮች ገለጹ።

በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ሁለተኛው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዛሬ ከንጋት 12 ሰዓት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ተካሂዷል፡፡

የኢራን አምባሳደር ሳማድ ላኪዛዴህ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ  ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባሻገር መርሐ ግብሩ ሌሎች ተጓዳኝ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ይህ ተጨባጭ ተግባርም ለሌሎች ሀገራት አርአያ ይሆናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ መላው ሕዝብ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እቅድን እውን ለማድረግ ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ የምታከናውነውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ማሳወቅና ማስገንዘብ እንደሚጠበቅባቸውም አመላክተዋል፡፡

በአንጻሩ የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መርሐ ግብሩን በመደገፍና በማገዝ ለስኬቱ ሊተባበሩ እንምደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በበኩላቸው÷ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሀገራት የፓሪስ ሥምምነት መፈረማቸውን እና የቀረው መተግበር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሀገራት ተጨባጭ ሥራ ከመስራት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ጠቅሰው ኢትዮጵያ እንደምታደርገው አይነት ሥራ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

በተጓዳኝ የዓለም ሥጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ሀገራት በመናበብና በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.