Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን የጥቁር ባህር የእህል ሥምምነትን ማራዘም በሚቻልበት አግባብ ላይ ከፑቲን ጋር ሊነጋገሩ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶኻን ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር የጥቁር ባህር የእህል ሥምምነትን ማራዘም በሚቻልበት አግባብ ላይ ሊነጋገሩ መሆኑን አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ ከፑቲን ጋር ውሉን ማራዘምና ማደስ በሚቻልባት አግባብ ላይ በስልክ ለመነጋገር ማቀዳቸውን አር ቲ ዘግቧል።

ሩሲያ በጥቁር ባህር በኩል የዩክሬን የጥራጥሬ ምርቶች ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ የተደረሰው ሥምምነት ‘አፈጻጸሙ ጉድለት አለበት’ በሚል ዳግም እንደማታድስ አስታውቃለች።

ሥምምነቱ ባለፈው አመት ሐምሌ ወር ላይ የተመድ፣ ሩሲያ፣ ዩክሬን እና የቱርክ ተወካዮች በተገኙበት ነበር የተደረሰው።

ከዚያን ጊዜ ወዲህም በተለያየ ጊዜ ሲራዘም ቆይቶ ሩሲያ ትናንት ገደቡ የሚያልቀውን ሥምምነት ማቋረጧን በመግለጽ እንደማታድስ ይፋ አድርጋለች።

ለዚህ ደግሞ ሞስኮ የምግብና የማዳበሪያ ምርቶቿን ለገበያ እንዳታቀርብ የሚያደርገውን የምዕራባውያንን ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ማንሳት አልቻለም በሚል ተመድን ወቅሳለች።

ይህ እስካልተተገበረ ድረስም ሩሲያ ለዚህ ሥምምነት ተገዥ እንደማትሆን የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል።

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም ተመድ እና ሞስኮ ሩሲያ ውሉን ለማራዘም ፍላጎት እንደሌላት መረዳታቸውን አረጋግጧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.