በሁሉም መስክ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ተናገሩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ በሁሉም መስክ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ተናገሩ፡፡
በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትርር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) የተመራው ቡድን በደቡብ ክልል ባደረገው የልማት ስራዎች የመስክ ምልከታ ሪፖርት ላይ ከክልሉ የካቢኔ አባላት ጋር ተወያይቷል፡፡
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ÷ በሁሉም መስክ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ ተጨማሪ መሬት በማረስ የተሻለ ምርት ለማግኘት ወደ እርሻ ለማስገባት ጥረት መደረጉን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ከግብርና ግብዓት ጋር በተያያዘ የአቅርቦትም ሆነ የመጠን ችግር እንዳጋጠመ አብራርተዋል።
ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ከ600 ሺህ ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት መቻሉንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውሰዋል።
ግብርናን ማዘመን ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ የመስኖ ተቋማትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ማለታቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)፥ በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በውይይት መድረኩ ከመስክ ምልከታው የተገኘውን መልካም ልምድ በማስቀጠል እና የታዩ ውስንነቶችን ፈጥኖ ማረም የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ፡፡