የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ።
የምክር ቤቱ ጉባዔ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሀምሌ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።
የምክር ቤቱ አፈጉባዔ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በጉባዔው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር÷ በክልሉ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት እና በመሰል የኢኮኖሚ ዘርፎች መልካም ጅምሮች መታየታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በኢኮኖሚ በማህበራዊ እና በመሰል ዘርፎች ላይ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይም ሕግን ከማስከበር፣ ተቋማዊ አሰራርን ከማጠናከር፣ የህዝብ ጥያቄን ከመመለስ እንዲሁም የመንግስት ወጭን በመጨመር ገቢን በማስፋት የክልሉን ልማት ለማጠናከር እንደሚሰራ አመላክተዋል።
ምክር ቤቱ በጉባኤ ቆይታው በ2015 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ላይ በመምከር የቀጣይ ዓመት እቅድ ላይ በመወያየት አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ እና ልዩ ልዩ ሹመቶችንም እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።
በክልሉ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ለማሻሻል የሃይማኖት አባቶች ሕብረተሰቡ እና ሁሉም የባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ሊሰሩ እንደሚገባም አፈጉባዔዋ አሳስበዋል፡፡
በለይኩን አለም