ፕሬዚዳንት ፑቲን በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የብሪክስ ጉባዔ ላይ አይሳተፉም ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን በመጪው ነኀሤ ወር በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የ”ብሪክስ” ጉባዔ ላይ እንደማይሳተፉ ተገለጸ፡፡
በፕሬዚዳንቱ ምትክ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የሚመራ ልዑክ በጉባዔው ላይ እንደሚገኝ ሜዱዛ ዘግቧል፡፡
የፕሬዚዳንቱ በጉባዔው ያለመሳተፍ ጉዳይ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የሁለትዮሽ ምክክር ከተደረገ በኋላ ውሳኔ ላይ መደረሱም ተመልክቷል፡፡
እንደሚታወቀው ደቡብ አፍሪካ የሮሙን ዓለም አቀፍ ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነትን አፅድቃለች፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ደግሞ በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ማዘዣ የወጣባቸው እንደመሆናቸው መጠን በደቡብ አፍሪካው ጉባዔ ላይ ቢገኙ ሀገሪቷ ይዛ ለሄግ አሳልፋ የመሥጠት ሕጋዊ ግዴታዋን መወጣት ይጠበቅባታል።
በዚህም ምክንያት ይመሥላል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከልዕለ-ኃያሏ ሀገር ሩሲያ ፕሬዚዳንት ጋር መክረው በጉባዔው ላይ እንዳይገኙ ውሳኔ ላይ የደረሱት፡፡
ብሪክስ በሚል መጠሪያ ጥምረቱን የመሠረቱት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ሲሆኑ አሁን አንዳንድ ሀገራት ቡድኑን ለመቀላቀል ፍላጎት እያሳዩ እና ማመልከቻቸውን እያቀረቡ ነው፡፡
ሀገራቱ ጥምረት የመሠረቱት በምጣኔ-ሐብት ፣ ንግድ እና ግብይትን በመሳሰሉ ጉዳዮች በትብብር ለመሥራት ዓላማ ሠንቀው መሆኑ ይነገራል፡፡