Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ ሰሞኑን በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከምሽቱ 1:00 ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12:00 ላልተወሰነ ጊዜ የሚተገበር የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ፡፡

ውሳኔው የተላለፈው የጋምቤላን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በማስመልከት የክልሉ ካቢኔ ዛሬ አመሻሽ ላይ ባካሄዱት አስቸኳይ ስብሰባ ነው።

በውሳኔው መሠረት÷ ከተመደቡ የጸጥታ ኃይሎች በስተቀር ከዛሬ ምሽት 1:00 ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12:00 ድረስ ማንኛውም ተሽከርካሪም ሆነ ሰው መንቀሳቀስ አይችልም፡፡

ከተመደቡ የፀጥታ አካላት ውጪ የትኛውንም ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም ተገልጿል።

በሌላ በኩል ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛም ሆነ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከነገ ጀምሮ መደበኛ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ካቢኔው ወስኗል፡፡

በክልሉ ለተፈጠረው የሰላም መደፍረስም እጃቸው ያለበት አመራሮች እና ሌሎች አካላት ተጠያቂ እንደሚደረጉ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የተጣሉ ክልከላዎችን በማክበርና በማስከበር ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ ካቢኔው አሳስቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.