Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የአደጋ ስጋት ተጋላጭነትን መሰረት ያደረገ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በክረምት ወቅት የሚያጋጥም የአደጋ ስጋት ተጋላጭነትን መሰረት ያደረገ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ገለጸ፡፡

በክልሉ 33 ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የመሬት መንሸራተት እና ጎርፍ አደጋዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ በዘንድሮ የክረምት ወቅት ከ450 ሺህ በላይ ወገኖች ለመሬት መንሸራተት እና ጎርፍ አደጋዎች ተጋላጭ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ወገኖች መካከልም በአደጋዎቹ ምክንያት እስከ መፈናቀል የሚያደርስ አደጋ ሊኖር ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

ይህን መሠረት በማድረግም ሊከሰት የሚችልን የጎርፍ አደጋ መጠን ለመከላከል እና ለመቀነስ የሚያግዝ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን እና አሁንም እየተሠራ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል፡፡

በክልሉ መንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ በ64 ሚሊየን ብር የጎርፍ አደጋ ሊከሰትባቸው ይችላል ተብለው የተለዩ የ20 አካባቢዎችን የመጥረግና የመገንባት ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡

በጣና ሐይቅ ዙሪያ የጎርፍ አደጋ ቢከሰት ለተፈናቃዮች ማጓጓዣ የሚሆኑ አምሥት ጀልባዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በክረምት ወቅት በጎርፍ ለሚፈናቀሉ ወገኖች መጠለያ በበጋ ወቅት ደግሞ እንደ ትምህርት ቤት የሚያገለግሉ ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ዞኖች ጎርፍ ቢከሰት ምን ሊደረግ ይችላል በሚል የመጠባበቂያ ዕቅድ አሰናድተው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወናቸውንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም የዓየር ትንበያ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ እያንዳንዱን ክስተት የመከታተል ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.