አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 8 ሺህ 642 ተማሪዎችን አስመረቀ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 13 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ መርሐ ግብር ያስተማራቸውን 8 ሺህ 642 ተማሪዎች አስመረቀ።
ከተመራቂዎቹ መካከል 5 ሺህ 121 በመጀመሪያ ዲግሪ ፣ 3 ሺህ 221 በሁለተኛ ዲግሪ እና 300 ተማሪዎች ደግሞ በሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች መሆናቸው ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደሐና (ፕ/ር) ለ73ኛ ጊዜ የተመረቁትን ተማሪዎች እና ወላጆቻቸውን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን የበለጠ ለማረጋገገጥ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቅድመ ምረቃ ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል 85 በመቶዎቹ የመውጫ ፈተናን አልፈው በዛሬው ዕለት መመረቃቸውን ተናግረዋል።
ባስተላለፉት መልዕክት “ኢትዮጵያ ያላትን ሰጥታ ከሌላት ላይ ተበድራ እናንተን አስተምራለችኋለች እናንተም በእውቀት፣ በሰላም እና ሕዝብን በማገልገል ውለታዋን እንድትከፍሉ እና ከፈተናዋ ልታሻግሯት ይገባል” ብለዋል።
ለሀገራችሁ እምርታ ለሕሊናችሁ እርካታን እንድታገኙ በበጎ ሥራዎች ላይ መሰማራት አለባችሁ ሲሉም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ እንዲሆን የተጀመረው ሒደት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል መጽደቁንም በዛሬው ዕለት አብስረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 34 ነጥብ 8 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።
በተመሳሳይም ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ እና በተከታታይና ርቀት ትምህርት መርሐ ግብር በ37 ፕሮግራሞች በቅድመ እና በድህረ ምረቃ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 309 ተማሪዎችን አስመርቋል።
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 286 ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ አስመርቋል።
ተመራቂዎቹ በመደበኛ እና በቅዳሜ እና እሁድ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል።
በአለምሰገድ አሳዬ፣ አዲሱ ሙሉነህ ፣ፍቅረሚካኤል ዘየደእና ማርታ ጌታቸው