ቻይና በ36 ቢሊዮን ዶላር በአልጄሪያ ውስጥ ኢንቨስትመንት ልታካሂድ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በ36 ቢሊዮን ዶላር በአልጄሪያ ውስጥ በተለያዩ መስኮች ኢንቨስትመንት ልታካሂድ መሆኑ ተገለጸ።
ሀገሪቱ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአዳዲስ ቴክኖሎጂ፣ በትራንስፖርት፣ በግብርናና ሌሎች መስኮች መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የኢንቨስትመንት ስራዎችን ልታከናውን እንደሆነ በቻይና የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት አብደልማጂድ ተቡኔ ይፋ አድርገዋል።
በቻይና ከሚኖሩ የአልጀሪያ ማህበረሰብ አባላት ጋር የተወያዩት ፕሬዚዳንቱ፤ “ከቻይና ጋር የተደረሰው የፕሮጀክት ስምምነት ግዙፍና ሁለቱን አገሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው” ብለዋል።
አልጀሪያ ከቻይና ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ጠቅሰው በቻይና ቆይታቸው ይህንን ለማሳካት የሚያስችል ተግባር ማከናወናቸውን እንደገለጹ የኒው አረብ ዘገባ አመልክቷል።