በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ዕጥበት ህክምና በመቋረጡ ታካሚዎች ለችግር መጋለጣቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 13 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ዕጥበት ህክምና በመቋረጡ ታካሚዎች ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸው ተገለፀ፡፡
ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሃሳባቸውን የሰጡ ታካሚዎች እንደሚሉት ÷ “ህይወታችን በህክምናው ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የአገልግሎቱ መቋረጥ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ምስቅልቅል አስከትሎብናል” ብለዋል፡፡
ታካሚዎቹ በግል የህክምና ተቋማት ህክምናውን ለማግኘት ያሉበት የኢኮኖሚ ደረጃ የሚፈቅድ ባለመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡
ከእጥበቱ ጎን ለጎንም የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማድረግ የጀመሩ ታካሚዎች ያሉ ሲሆን በተፈጠረው ችግር ምክንያት ህክምናው እንዳይስተጓጎልባቸው ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል፡፡
ሆስፒታሉ በበኩሉ የአገልግሎት መስጫ ቁሳቁስ ለጥገና መቆሙ እንዲሁም ያጋጠመው ከፍተኛ የሆነ የመድሃኒት እጥረት በስራው ላይ እንቅፋት መሆኑን አስታውቋል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ ፕሮቮስት ዶክተር ሲሳይ ስርጉ÷ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጥባቸው መሳሪያዎች ጥገና ስላስፈለጋቸው መለዋወጫዎች ገብተው የመሳሪዎችን ጥገና ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም ባጋጠመው ከፍተኛ የሆነ የመድሃኒት እጥረት የተወሰኑ ታካሚዎችን ወደ ዳግማዊ ሆስፒታል ኩላሊት እጥበት ማእከል ሄደው አገልግሎቱን እንዲገኙ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበቱን የሚያገኙ ታካሚዎች መድሃኒቶቹ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይሄዱላቸው እንደነበር ያስረዱት ዶክተር ሲሳይ፥ አሁን ግን ግዥ እስከሚፈፀም ድረስ መድሃኒት በመጥፋቱ አገልግሎቱ መቋረጡን ተናግረዋል።
የታካሚዎችን ችግር ለመቅረፍም በጊዜያዊነት አሁንም ከዘውዲቱ ሆስፒታል ለኩላሊት እጥበት ህክምና አገልግሎት የሚውል መድሃኒት በመገኘቱ አገልግሎቱን ዳግም ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በሰሎሞን ይታየው