የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ በተከሰሱበት ወንጀል የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላለፈ።
በእነ አቶ በረከት ስምዖን የክስ መዝገብ የተከሰሱት አንደኛ ተከሳሽ አቶ በረከት ስምዖን፣
ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ታደሰ ካሳ እና ሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ግዛው በዐቃቤ ሕግ በቀረቡባቸው አራት ክሶች ሲከራከሩ መቆየታቸው ይታወቃል።
ተከሳሾች ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በነበሩ የሥራ ውሎች የጥረት ኮርፖሬትን ጥቅም በሚጎዳ መንገድ ተንቀሳቅሰዋል የሚሉ አራት ክሶች ቀርበውባቸዋል።
ሁሉም ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈጸምንም፤ ጥፋተኛም አይደለንም ሲሉ ክደው መከራከራቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ባዋለው ችሎት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል።
በዚህም አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ ጥፋተኛ ሲባሉ ሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ግዛው ከቀረቡት ክሶች ነፃ ናቸው ተብሏል።
ፍርድ ቤቱ የቅጣት አስተያየት ለማዳመጥ ለሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ኢብኮ ዘግቧል።