ቢዝነስ

ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቅመማቅመም ከ10 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

By ዮሐንስ ደርበው

July 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ 6 ሺህ 323 ቶን ከቀረበ የቅመማ ቅመም ምርት 10 ነጥብ 48 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ፡፡

ለውጭ ገበያ ከተላኩ ዋና ዋና የቅመማ ቅመም ምርቶች መካከልም÷ በሶብላ፣ ኮረሪማ፣ አዝሙድ፣ በርበሬ፣ አብሽ፣ ዝንጅብል፣ ጥምዝ፣ ድንብላል፣ ጦስኝ፣ ቀረፋ እና ዕርድ እንዲሁም ሌሎች ይገኙበታል፡፡

ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጀምሮ ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል፣ የምርት ጥራት አጠባበቅ ላይ ተገቢውን ስልጠና መስጠትና የወጪ ንግዱን የሚመጥን በቂ ምርት እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ለምርት ዝግጅት ጥቅም ላይ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች ለምርት ጥራት እና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ÷ በተጠቃሚዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የግብዓት እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም መፍጠር ላይ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው÷ ግብይቱ በሕግ ማዕቀፍ እንዲደገፍ እና ተዋንያኑም ሥርዓቱን እንዲከተሉ ለማስቻል የአፈጻጸም መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

በዮሐንስ ደርበው