ጣሊያን ክልከላዎችን ስታላላ በጀርመን ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እየተመለሱ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 26 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጣሊያን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ጥላው የነበረችውን ጥብቅ ክልከላ ማላላት ጀምራለች።
ሃገሪቱ ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ በቫይረሱ ሳቢያ ማንኛውንም እንቅስቃሴ አግዳ መቆየቷ የሚታወስ ነው።
አሁን ላይም ከአውሮፓ ሃገራት ክልከላውን በማላላት ቀዳሚዋ ሃገር ሆናለች።
ክልከላው በቫይረሱ ሳቢያ አዲስ የሚያዙ እንዲሁም ህይዎታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ መላላት ጀምሯል ነው የተባለው።
ይህን ተከትሎም ከ4 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ሰዎች ወደ ስራ ተመልሰዋል፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግም ግዴታ ነው።
ጣሊያን በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ከአውሮፓ ሃገራት በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳች ሃገር ናት።
በቫይረሱ ሳቢያም ከ29 ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።
ከጣሊያን ባለፈም በግሪክ የተወሰኑ ክልከላዎች የተነሱ ሲሆን፥ በጀርመንም ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት አምርተዋል።
ከዚህ ባለፍ የተወሰኑ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም ደንበኞቻቸውን ለማስተናገድ እየተዘጋጁ መሆኑን ዘገባዎች ያመላክታሉ።
ምንጭ፦ ቢቢሲ እና አልጀዚራ