Fana: At a Speed of Life!

የውጭ አገራት የጉዞ ታሪክ ሳይኖራቸው የኮሮናቫይረስ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ አገራት የጉዞ ታሪክ ሳይኖራቸው የኮሮናቫይረስ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ፡፡

ሚኒስትሯ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ሳይኖራቸው በቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ መዘናጋት አይገባም ብለዋል።

ኅብረተሰቡ በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር “አነስተኛ ነው” በማለት እየተዘናጋ ነው ብለዋል።

በጎረቤት አገራት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑንም ገልጸው ይህም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

ሳይንሳዊ ምርምሮችም የቫይረሱ ስርጭትም ሊጨምር እንደሚችል እያሳዩ መሆኑን ጠቁመው ኅብረተሰቡ ሳይዘናጋ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ምክራቸውን ለግሰዋል።

የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በአርቲስቶችና በተለያዩ አካላት እየተሰሩ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል በተለያዩ አካላት የሚደረጉትን ድጋፎች መንግሥት በአድናቆት እንደሚመለከተው ገልጸው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ቫይረሱን ለመከላከል በዜጎችና አገር በቀል ድርጅቶች አዳዲስ ሃሳቦች የመከላከያ አልባሳትና ቁሳቁሶች በስፋት እየተመረቱ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህን የፈጠራ ሥራዎች ከሚመለከተው የመንግሥት አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሳደግና ማጎልበት እንደሚገባ ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።

አገር በቀል ድርጅቶች የኮሮናቫይረስና ሌሎች በሽታዎችን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውሉ መሣሪያዎችን እየጠገኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

ድርጅቶቹ እነዚህን መሣሪያዎች በቀጣይ በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ ሥራዎች እያከናወኑ መሆኑን አስረድተው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በተጓዳኝም የጤና ተቋማት ለእናቶችና ለህጻናት ጤና ጨምሮ ለሌሎች በሽታ የሚሰጠው አገልግሎት እንዲጠናከር ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.