Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ 200 የሚጠጉ ወረዳዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በያዝነው የክረምት ወቅት ለጎርፍ፣ ናዳ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 200 የሚጠጉ ወረዳዎች እና ዞኖች ተለይተው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የተለያየ መጠን ያለው ተጋላጭነት መኖሩን የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አታለለ አቡሃይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አረጋግጠዋል፡፡

ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች መለየታቸውን ተከትሎም በሕብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ በሥራ ላይ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡

ቀዳሚው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ በመሆኑ ስትራቴጅክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የፌደራል እና የክልል መንግሥታትም በክረምት ወቅት ሊደርሱ በሚችሉ አደጋዎች እና ቅድመ ጥንቃቄ ላይ መመካከራቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ከፍተኛ የተጋላጭነት ስጋት ያለባቸው ነዋሪዎችም ለጊዜው ከመኖሪያቸው ወደ ሌላ ቦታ እንዲያርፉ መደረጉን ነው አንስተዋል፡፡

በያዝነው የክረምት ወቅትም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ 1 ነጥብ 5 ወገኖች ለጎርፍ እና ተያያዥ ችግሮች ተጋላጭ ስለመሆናቸው ነው ያመላከቱት፡፡

ከእነዚህ መካከል ጉዳት ለደረሰባቸው 500 ሺህ ወገኖች÷ ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች ድጋፍ እየቀረበ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል፡፡

ሕብረተሰቡ እራሱን በመጠበቅ የሚተላለፉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በመተግበር እራሱን ከክረምት ወቅት ከአደጋ እንዲጠብቅም አሳስበዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.