ሕገ ወጥ ስደትንና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ድህነትን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ግልጽ ተግባራት ያስፈልጋሉ-ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ሕገ ወጥ ስደትንና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት እንዲሁም ድህነትን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ግልጽ ተግባራት ያስፈልጋሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጣልያን ሮም እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የልማት እና የፍልሰት ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፉ ነው።
ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷”ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በሰበሰቡት ዓለም አቀፍ የልማት እና የፍልሰት ኮንፈረንስ ላይ ዛሬ ተካፍያለሁ” ብለዋል።
ሕጋዊ የውጭ ሥራ ሥምሪት በሕጋዊ መልኩ ለወጡ የሥራና መተዳደሪያ ምንጭ፣ ለትውልድ ሀገራቸውም የሬሚታንስ ምንጭ ነው ሲሉም አስፍረዋል።
ሕገ ወጥ ስደትንና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ድህነትን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ግልጽ ተግባራት እንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል፡፡
ለሥራ ፈጠራ መዋዕለ ንዋይን ማመቻቸት ይገባል፤ ለስደት በሚዳርጉ መነሻ ምክንያቶች ላይ መሥራትም ተገቢ ነው ሲሉም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ካላት ስትራቴጂካዊ አቅም አንጻር የስደት ምንጭ መሸጋገሪያ እና መድረሻ መሆኗ ተገልጿል።
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ የስደት አስተዳደርን ለማጎልበት፣ ሕገ ወጥ ስደትን እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመፍታት በርካታ የፖሊሲ፣ የሕግ እና ተቋማዊ እርምጃዎችን መወሰዷን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡