Fana: At a Speed of Life!

በአሁኑ ወቅት የአገር ሉአላዊነትና የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ የመንግስት ቀዳሚው ጉዳይ ነው-የመንግስት የስራ ኃላፊዎች

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 26 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሁኑ ወቅት የአገርን ሉአላዊነትና የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ የመንግስት ቀዳሚው ጉዳይ መሆኑን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተናገሩ።

ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የአገርን ብሄራዊ ጥቅምና የህዝብን ህልውና ለውጭ ኃይል አሳልፎ መስጠት አግባብ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብርሃ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በኮሮና ቫይረስና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በአሁኑ ወቅት የአገርን ሉአላዊነትና የህዝብን ደህንነት የማረጋገጥ ጉዳይ የመንግስት ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት ሃላፊዎቹ በተለይም የህዝቡን ጤንነት መጠበቅና የህዳሴው ግድብን ማጠናቀቅ ቅድሚያ የሚሰጣቸው አጀንዳዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የአገርን ብሄራዊ ጥቅምና የህዝብን ህልውና ለውጭ ሃይል አሳልፎ መስጠት አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መንግስት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል፣ የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅና የዴሞክራሲ ባህል እንዲዳብርና የአገርን ሉአላዊነት የማስጠበቅ ስራዎችን እየሰራ ለውጥም እየታየ ነው ብለዋል።

“እኛ አጀንዳችን ህዝብ የማዳን” ነው ያሉት ሃላፊው፤ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ አጠናቆ  ውሃ በመሙላት  ሀገሪቱን ከችግርና ድህነት መውጫ መሳሪያ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀምም ሃይል የተሞላበት ሳይሆን የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማይጫንና በህግ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ሊያስወቅስ አይገባም ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ስለ ምርጫና ስለ ፖለቲካ የተለያዩ ሃሳቦች መነሳታቸው እንደ ሃሳብ ጤናማ ቢሆንም ከሃሳብ አልፈው የህዝብንና የአገርን ብሄራዊ ጥቅም የሚጎዱ መሆን የለባቸውም ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝብ ብጥብጥና ግጭት ሰልችቶታል፣ይህንን ሃሳብ የሚቀበልበት ጊዜም አይደለም “ያሉት አቶ ንጉሱ፤ መንግስት የህዝብን ደህንነትና የአገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮችን እንደየመልካቸው ይመልሳል በማለት ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት ምርጫ እናካሂድ ማለት “አንተ እየሞትክ እኔ ልመረጥ ማለት ነው” ያሉት ደግሞ አቶ ዛዲግ አብርሃ ሲሆኑ ከሁሉም በፊት የህዝብ ደህንነትና የአገር ሉአላዊነት ይቀድማል ሲሉ ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን የጤና ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጫና በመከላከል በኩል እስካሁን ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ነአስረድተዋል።

“ሰራተኛው ከስራ እንዳይፈናቀል፣ተቋማት እንዳይሞቱ እንደግፍ በሚል መንግስት የተቋማትን እዳ ፣የግብር እዳ ሰርዟል፣ተጨማሪ ፋይናንስ ወደ ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል፣ሰራተኞች እንዳይበተኑ የታክስ እፎይታ ተሰጥቷል” ነው ያሉት።

እነዚህ ሁሉ ማሻሻያዎች  ኢኮኖሚው ብዙ ሳይጎዳ የበሽታውን ችግር ለማለፍ ያግዛል በማለት፤ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉና የኮሮና ቫይረስ በሽታ በአጭር ጊዜ ከቆመ ኢኮኖሚው ብዙም ሳይጎዳ እንደገና አንሰራርቶ የእድገት መስመራችንን መቀጠል አንችላለን  ነው ያሉት ዶክተር እዮብ።

መንግስት የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል አኳያ ጥሩ ውጤት እያመጣ ቢሆንም የቫይረሱ ስርጭት በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል መታየቱ የሚያስደነግጥ መሆኑንና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎቹ አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.