79ኛው ዓመት የኢትዮጵያውያን አርበኞች የድል በዓል ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 79ኛው ዓመት የኢትዮጵያውያን አርበኞች የድል በዓል በዛሬው እለት ተከብሮ ውሏል።
በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሀውልት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ እና የአባት አርበኞች ተወካዮች ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የድል በዓልን በማስመልከት ትናንት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት፥ በኮቪድ-19 ስጋት የተነሳ እንደለመድነው በአርበኞች ሀውልት ዙሪያ አንድ ላይ ተሰባበስበን በዓሉን ማክበር ባንችልም፤ የእነዚያን የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆችን ዘመን የማይሽረው ተጋድሎ በመንፈስ አድምቀነው እንደምንውል እምነቴ ጽኑ ነው ብለዋል።
የአድዋ እና የአርበኞችን ድል መንፈስ እየታደሰ የሚቀጥል ህያው መንፈስ ማድረግ አለብን ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ ለዘላቂ የሀገራችን ጥቅሞች ልናውላቸው ይገባናል ሲሉም ገልፀዋል።
“በታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሳየነውን አንድነትና ታላቅ ህልም በሌሎችም ላይ እናባዛው፤ ዛሬ በተለያየ መልኩ የተደቀኑብንን ፈተናዎች ድል ለመንሳት እናውላቸው” ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኮቪድ-19 የደቀነብን አደጋ ከማይታይ ጠላት ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፤ የቫይረሱ ተለዋዋጭ ሁኔታ ሥራችንን ሁሉ ዱካውን ያጠፋ ጠላት ያህል ፈታኝና ውስብስብ አድርጎብናል፤ መመሪያ አክብረን፣ የሚጠበቅብንን ተወጥተን እስከተፋለምነው ድረስ ለመቆጣጠር ያለንን ዕድል ያሰፋዋል፤ ከወረርሽኙ በኋላ የሚኖረውን ሁኔታ ከአሁኑ የተሻለ ለማድረግም የቤት ስራችንን መጀመር ይኖርብናልም ብለዋል።
ጣሊያን የአድዋን ድል ለመበቀል በሚል በጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቤኒቶ ሙሶሎኒ አማካኝነት፥ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን መውረሯ የሚታወስ ነው።
በወቅቱ የነበሩት ኢትዮጵያውያንም ወራሪውን ሀይል ለአምስት ዓመታት በጽናት ታግለው 1933 ዓ.ም ድል ነስተውታል።
የወቅቱ አርበኞች ለሀገራቸው ነጻነት የከፈሉትን መስዋዕትነት እና ያስገኙትን ድል ለማሰብም፤ በየአመቱ ሚያዚያ 27 ተከብሮ ይውላል።