Fana: At a Speed of Life!

‘ሌባ ነው’ ያሉትን ግለሰብ ደብድበው የገደሉ 6 ተከሳሾች በጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘ሌባ ነው’ ያሉትን ግለሰብ ደብድበው የገደሉ ሥድስት ተከሳሾች ከ10 እስከ 11 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት መቀጣታቸው ተገለጸ፡፡

ከእስራቱ በተጨማሪ የሁሉም ተከሳሾች ሕዝባዊ መብቶች ለ2 ዓመት መሻራቸው ተገልጿል፡፡

1ኛ ዓለሙ መለሰ፣ 2ኛ ታከለ አበራ፣ 3ኛ ብርሌው ጫኔ፣ 4ኛ ዋቁማ ልሳኑ፣ 5ኛ አስቻለው ታደለ፣ 6ኛ ደሳለኝ መንግስቴ የተባሉ ተከሳሳሾች ለጊዜው ካልተያዙ ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን ወንጀሉን መፈጸማቸውን በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡

ታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 8፡40 በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 አይ ሲ ቲ ፓርክ ግቢ ውስጥ ሟች ለታ ዳዲን ሊሰርቅ ግቢ ውስጥ ገብቷል በሚል ምክንያት÷ 1ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ ተከሳሾች እና አንድ ያልተያዘ ግብረአበራቸው ለጥበቃ በያዙት የእንጨት ዱላ መደብደባቸው ተገልጿል፡፡

2ኛ ተከሳሽ እና ያልተያዘ ግብረአበራቸው ሟችን በመደብደብ በሽቦ ሁለት እግሮቹን በማሰር ሕይወቱ እንዲያልፍ በማድረጋቸው ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የግድያ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች የተከሰሱበት ክስ በችሎት ተነቦላቸው የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ይሁንና ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን አቅርቦ ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በማስረዳቱ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ብይን መስጠቱን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ተከሳሾችም በቀረበባቸው ክስ መሰረት የመከላከያ ምስክር አቅርበው ቢያሰሙም ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ይከላከሉ በተባለበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚህም 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በ10 ዓመት ጽኑ እስራት 4ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች በ11 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.