27 የተሰረቁ ካሜራዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያየ መጠንና የስሪት ምልክት ያላቸው 27 የተሰረቁ ካሜራዎች መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
ካሜራዎቹ የተያዙት ትናንት ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ይርጋ ሃይሌ የገበያ ማዕከል የካሜራ ጥገና ሱቅ ውስጥ ነው።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ህገወጥ ድርጊትንና ወንጀልን ለመከላከል እንዲሁም ለመቆጣጠር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ህጋዊ የንግድ ፍቃድን ሽፋን በማድረግ ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰረቁ ካሜራዎችን እየተቀበለ በርካሽ ዋጋ የሚሸጥ ግለሰብ መኖሩን ፖሊስ በማስረጃ ማረጋገጡን አመልክቷል።
ፖሊስ በህግ አግባብ ባደረገው ፍተሻ የተለያዩ መጠን ያላቸው 27 የተሰረቁ የቪዲዮና የፎቶ ካሜራዎችን መያዙ ታውቋል።
በተያዘው ግለሰብ ላይ አስፈላጊው ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ ፖሊስ አመልክቶ፤ የተሰረቀ እቃ በሚገዙ ላይ የጀመረው የቁጥጥር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
ከዚህ ቀደም ካሜራ የተሰረቀባቸው ግለሰቦች አዲስ ከተማ ከፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመቅረብ ንብረቶቻቸውን እንዲመርጡ ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል ።