ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የአልባሳት ግዢ ጋር ተያይዞ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃን ጨምሮ በስምንት ሰራተኞች ላይ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የአልባሳት ግዢ ጋር ተያይዞ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።
ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ 1ኛ የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃ፣ 2ኛ የተቋሙ የመንግስት የግዢ ዳይሬክተር ግሩም ወልዴ፣ 3ኛ የኮሚሽኑ የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት ባለሙያ ደረጄ ተፈራ፣ 4ኛ የኮሚሽኑ የሎጀስቲክስ ምዝገባና ቁጥጥር ባለሙያ ወንድሜነህ ምስጋናው፣5ኛ የአደጋ ስጋት ትግበራ ቡድን መሪ እዮብ ታደሰ ካሳ ፣6ኛ በኮሚሽኑ የህክምና ባለሙያዋ ሲስተር አልማዝ ጌቶ፣ 7ኛ የአደጋ መረጃ ሀርድ ዌርና ሶፍትዌር ባለሙያ መስፍን ለገሰ እና 8ኛ ነጋዴ የሆኑት ንጉስ አማን የተባሉ ተከሳሾች ናቸው ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
በዚህ በቀረበ ክስ ላይ እንደተመላከተው በሰኔ ወር በ2014 ዓ.ም በጀት አመት ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች የግዢ ጨረታ ሂደት ውስጥ በመሳተፍ በስውር በመመሳጠር በወቅቱ በተደረገ የገበያ ዳሰሳ ጥናት የአልባሳቱ ዋጋ 46 ሺህ 923 መሆኑ እየረጋገጠ ተከሳሹቹ ግን ብልዶዘር የተሰኘ የእሳት አደጋ መከላከያ ልብስን ከፍተኛ በሆነ ዋጋ ማለትም በፍሬ 184 ሺህ 644 ብር ከ8ኛ ተከሳሽ ተጫራች ድርጅት ግዢ እንዲፈጸም በማፅደቅ አጠቃላይ 217 ፍሬ አልባሳትን በ40 ሚሊየን 67ሺህ 748 ብር በመግዛት በመንግስት ላይ በልዩነት 29 ሚሊየን 885ሺህ 441 ብር ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብሎ ነው በክስ ዝርዝሩ የቀረበው።
በዚህም ተከሳሾቹ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ፣ለ እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007/አንቀጽ 9(1) ሀ እና ለ ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ያለአግባብ ግድፈት በመገልገል 8ኛ ተከሳሽ ደግሞ የወንጀሉ ልዩ ተካፋይ በመሆኑ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ከተከሳሾቹ መካከለል 1ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ያልቀረቡ ሲሆን ÷ቀሪ ስድስት ተከሳሾች ግን ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
ተከሳሾቹ ከጠበቃ ጋር ተማክረው እንዲቀርቡ በይደር ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ