ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሥደተኞች ቁጥር ከ68 ሺህ ተሻገረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በሱዳን የተከሰተውን ግጭት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሥደተኞች ቁጥር ከ68 ሺህ ማለፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ፡፡
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ እንዳስታወቀው ፥ በሱዳን ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በዚህ ዓመት እስከ ፈረንጆቹ ሚያዝያ ወር አጋማሽ ድረስ 68 ሺህ 601ሥደተኞች መድረሱን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል።
ከአጠቃላይ ከሱዳን ተመላሽ ሥደተኞች መካከል 49 በመቶ ያህሉ በዚያው ሲኖሩ የቆዩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
ሱዳናውያን ሥደተኞች 30 በመቶውን እንደሚይዙ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
እስከ ዛሬ ጦርነቱን ‘‘አንተ ነህ የጀመርከው የለም አንተ ነህ’’ በሚል ውዝግብ ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች እየተወነጃጀሉ እንደሚገኙም ተመላክቷል፡፡