Fana: At a Speed of Life!

ሰሜን ምዕራብ ዕዝ ለውጥ የወለደው የመከላከያ ቀኝ እጅ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ምዕራብ ዕዝ በአስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ለውጥ የወለደው የመከላከያ ቀኝ እጅ ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የዕዙ ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም ውይይት ማጠቃለያ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ሰሜን ምዕራብ ዕዝ የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ጀግንነት የፈፀመና በርካታ ጀግኖችን ያፈራ ታሪክ ሠሪ ዕዝ ነው ብለዋል።

ዕዙ በአስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ለውጥ የወለደው የመከላከያ ቀኝ እጅ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሌም በሚፈፅመው ተልዕኮ የሚያኮራ ዕዝ ነው በማለት ገልጸዋል።

ዕዙ የተሰጠው ተልዕኮ ኢትዮጵያን ማቆየትና ማሻገር እንደሆነ አስገንዝበው፤ ለዚህም ሠራዊቱን በስነ-ልቦናና በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ማብቃት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

ተልዕኳችሁንም በገለልተኝነት፣ ስብዕናን በመላበስ፣ ዲሲፕሊን በማክበርና በውጤታማነት በመፈፀም የፕሮፌሽናል ሠራዊት ባህሪን መላበስ ይገባል ማለታቸውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት መረጃ አመልክቷል።

በዕለቱም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላና የዕዙ አመራሮች በጠቅላይ መምሪያው ቅጥር ጊቢ ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.