በሐረሪ ክልል ሁሉም አመራሮች የተሳተፉበት የግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉበት የግምገማ መድረክ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አብዱጀባር መሐመድ የግምገማ መድረኩን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም÷ መድረኩ በበጀት ዓመቱ የተሠሩ ዋና ዋና የፓርቲ ተግባራትና አፈፃፀም ላይ እንደሚያተኩር አንስተዋል፡፡
አመራሩ በጠራ የአመለካከት አንድነት ሕዝቡን ከጎኑ አሰልፎ የተናበበ እንቅስቃሴ በማድረጉ በርካታ ፈተናዎችን በመሻገር አበረታች ስኬቶች መመዝገባቸውንም ገልፀዋል።
የፓርቲውን ተግባራት አፈፃፀም በመገምገም ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ጉድለቶችንም በማረም ጠንካራ የፓርቲ አመራር መፍጠርን መሠረት ያደረገ መድረክ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል፡፡
የአመራሩ ኃላፊነትን በብቃት ከመወጣት፣ የመሪነት ሰብዕና እና ሥነ-ምግባር ከመላበስ አንጻር እንደ ፓርቲ የተጣለበትን ግዴታ በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን የሚረጋገጥበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
የግምገማ መድረኩ ሌብነትን፣ ፅንፈኝነትን እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በተደራጀ አግባብ ታግሎ ለማስተካከል ያስችላል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
የሥነ- ምግባር ችግር ያለባቸው አመራሮች በመድረኩ ተጠያቂ እንደሚሆኑም አረጋግጠዋል፡፡