Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ኢኮኖሚ መስከን እያሳየ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ኢኮኖሚ መስከን እያሳየ መሆኑን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ገለጸ፡፡

ዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) አሻሽሎ ባወጣው ሪፖርቱ የዓለም ኢኮኖሚ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ባጋጠሙ የተለያዩ እክሎች ምክንያት ቀውስ ገጥሞት መቆየቱን አስታውሷል።

የኮሮና ወረርሽኝ፣ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ጫናዎች የዓለም ኢኮኖሚ እንዲናጥ ዋና ምክንያቶች ነበሩ።

በተጋመሰው ይህ የአውሮፓውያኑ ዓመትና ተከትሎ በሚመጣው የፈረነረጆቹ 2024 አዲስ ዓመት የዓለም ኢኮኖሚ ከመናጥ ወጥቶ እየሰከነ እንደሚሄድ የአይ ኤም ኤፍ መረጃ ማመላከቱ ተገልጿል።

ይሁንና የዓለም ኢኮኖሚም ሆነ በየቀጣናው የሚመዘገቡ የኢኮኖሚ ዕድገቶች አዝጋሚ ሆነው ነው የሚቀጥሉት ሲል የተከለሰው መረጃው አክሏል።

ዓምና አይ ኤም ኤፍ ባሠፈረው ቅድመ-ግምት የዚህ ዓመት የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት 3 ነጥብ 5 በመቶ ይሆናል የሚል ነበር።

ይሁንና አሁን በተከለሰው ግምት መሠረት ግን ቀድሞ ከተገመተው ባነሰ 3 ነጥብ 0 በመቶ እድገት ነው እንደሚመዘገብ የሚጠበቀው።

አይ ኤም ኤፍ የተከለሰውንና የዓለም ክፍለ-አህጉራዊና ቀጣናዊ የ2023 እና 2024 የኢኮኖሚ እመርታ ቅድመ-ግምቱን በትናንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል።

ምንም እንኳ የኢኮኖሚ ስክነት እየሰፈነ የሚመጣ ቢሆንም÷ አሁንም ሁኔታው ከሀገር ሀገር የተለያየ መገለጫ እንደሚኖረውና ፈተናዎችና ችግሮችም አብረው እንደሚዘልቁ የሚጠበቅ መሆኑንም ነው አይ ኤም ኤፍ በሪፖርቱ ያመላከተው።

በመሆኑም የየሀገራቱ መንግስታትና ብሄራዊ ባንኮቻቸው ዋነኛ ትኩረታቸውን የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ፣ የፋይናንስ እንቅስቃሴን የተረጋጋ ማድረግና መሠል የሞኒታሪና የፊስካል ርምጃዎች ላይ እንዲያተኩሩ አሳስቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.