ደህንነት ነኝ በማለት ግለሰቦችን በማስፈራራት ገንዘብ ሲቀበል ነበር የተባለ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ቀረበ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መታወቂያ በማዘጋጀት ደህንነት ነኝ በማለት ግለሰቦችን በማስፈራራት ገንዘብ ሲቀበል ነበር የተባለ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ቀረበ።
ተጠርጣሪው ነስሩ ሳሌ ጀማል ይባላል።
ግለሰቡ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሰራተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት ደህንነት ነኝ በማለት ግለሰቦችን በወንጀል እንደሚፈለጉ በመግለፅ እና መታወቂያውን በማሳየት በማስፈራራት ከተለያዩ ግለሰቦች እስከ 200 ሺህ ብር የደረሰ ገንዘብ መቀበሉን የጠቀሰው የፌደራል ፖሊስ መርማሪ በዚህ መነሻ በክትትል በቁጥጥር ስር መዋሉን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት አስረድቷል።
በዚህም መሰረት ምርመራውን በሰውና በሰነድ አጠናቅሮ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 59/2 መሰረት ፍርድ ቤቱ የ14 ቀን የማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
ተጠርጣሪው ወንጀሉን መፈጸሙን በማመን የዋስትና መብቱ እንዲከበር ችሎቱን ጠይቋል።
የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ተጨማሪ ማጣሪያ የማድረግ አስፈላጊነትን በማመን ለፖሊስ የ14 ቀን የማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ