የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት (ፋኦ) ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ ጋር ያለው ትብብር ይበልጥ በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ።
ግርማ አመንቴ ዶ/ር) በቅድሚያ ዋና ዳይሬክተሩ ለሁለተኛ ዙር በመመረጣቸው ደስታቸውን ገልጸው÷ ኢትዮጵያ ከዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት ጋር ጠንካራና ለረጅም ጊዜ የቆየ ትብብር እንዳላት ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ትብብር ይበልጥ እንዲጠናከር በቅርበት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በተለይ በበርሃ አንበጣ ወረርሺኝ መከላከል፣ በእንስሳት ልማትና በስርዓተ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ዘርፎች ያለው ትብብር ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በግርብርናው ዘርፍ ትልቅ መነሳሳት እንደተፈጠረ ጠቅሰው÷በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በርካታ ኢንሼቲቮች መተግበራቸውንና አበረታች ውጤቶች ማስገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረትና በተሰራው ስራ የተገኘው ውጤት የሚደነቅና ተስፋ ሰጭ መሆኑን አስታውሰዋል።
ለግብርና ሜካናይዜሽን፣ ለአርሶ አደሮች አገልግሎትና ለግብርና ግብዓት አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ የበለጠ ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም ተናግረዋል።
ድርጅቱ በቀጣይም ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል ጥሪ መቅረቡን የሚስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡