Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ፑቲን በሩሲያና አፍሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቃል ገቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሀገራቸው እና አፍሪካ መካከል ያለውን የንግድ፣ የኢኮኖሚ እና ሰብአዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቃል ገብተዋል።

ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በሩሲያ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በጉባኤው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ታድመዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ፑቲን በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ÷የሩሲያ-አፍሪካ የንግድ ልውውጥ 18 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ገልጸዋል።

በፈረንጆቹ 2023በሩሲያ እና በአፍሪካ መካከል የግብርና ምርቶች ንግድ 60 በመቶ ማደጉን ጠቁመው÷ “በቀጣይ የጋራ የንግድ ግንኙነቱን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንችላለን” ብለዋል፡፡

ሩሲያ በ2023 በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ሩሲያ 10 ሚሊየን ቶን እህል ወደ አፍሪካ ልካለች ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ፑቲን።

በቀጣይ ሶስት እና አራት ወራት ውስጥም ለቡርኪናፋሶ፣ ዚምባቡዌ፣ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ሌሎች ሀገራት ከ25 ሺህ እስከ 50 ሺህ ቶን እህል በነፃ ለማቅረብ ዝግጁ እንደሆነችም አረጋግጠዋል፡፡

የሩሲያ ኢኮኖሚ ህብረት ልምዱን ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና መድረክ ለማካፈል መዘጋጀቱን ጠቁመው÷በዚህም አህጉሪቱ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አቅሟን ለማሳደግ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በግብፅ ስዊዝ ካናል አቅራቢያ የሚገኘው የሩሲያ የኢንዱስትሪ ዞን በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር እና ምርቶቹን ወደ አፍሪካ መላክ እንደሚጀምር ጠቅሰዋል፡፡

ሩሲያ የአፍሪካን የፋይናንስ መሠረተ ልማት ለማዳበር እና ከሩሲያ የክፍያ ስርዓት ጋር ለማገናኘት ዝግጁ መሆኗንም አንስተዋል፡፡

ሩሲያ የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ማዕቀፍ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ 35ሺህ የሚጠጉ አፍሪካውያን ተማሪዎች በሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች እየተማሩ ሲሆን÷ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡

በወንደሰን አረጋኸኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.