Fana: At a Speed of Life!

የአድዋ አዋርድ አዘጋጅ ሰለሞን ገለታ በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል ተከሰሰ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአድዋ አዋርድ አዘጋጅ ሰለሞን ገለታ ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል ተከሰሰ።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ተከሳሹ የወንጀል ህግ የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 2 እና 3 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በማለት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦበታል።

በዚህ በቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሹ የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ሰዓት ገደማ በቂርቆስ ክ/ከ ወረዳ 10 እስታዲየም የኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከል ውስጥ ከኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከ ወረዳ 4 ወሳኝ ኩነት ቅርጫፍ ጽ/ቤት ያልተሰጠ ሀሰተኛ መታወቂያና ከንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ ያልተሰጠ ሀሰተኛ አቤል ጫላ አስመጪና ላኪ በሚል ሒሳብ ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ሒሳብ 167 ሺህ 750 ብር ገቢ ያደረገ መሆኑን የሚገልጹ ሀሰተኛ ሰነድ ደረሰኝ ይዞ በመቅረብ ከኢትዮ ቴሌኮም 2 ሳምሰንግ ታብሌቶችን የወሰደ መሆኑ ተጠቅሶ በክሱ ላይ ተዘርዝሯል።

በሁለተኛው ደግሞ በመጋቢት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ሰዓት ገደማ በአራዳ ክ/ከ በቸርችል ጎዳና በኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ማዕከል በመገኘት ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በመጠቀም፥ በንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርጫፍ በኤም ኤም ዲ ኤ ትሬዲንግ ስም ከተከፈተ ሒሳብ ወደ ኢትዮ ቴሌኮም 279 ሺህ 460 ብር ገቢ ያደረገ መሆኑን የሚገልጽ ሀሰተኛ የገቢ ደረሰኝ ይዞ መቅረቡ ተጠቅሷል።

በዚህም ሀሰተኛ ሰነዶችን በመገልገል 2 ሳምሰንግ ጋላክሲ ሞባይሎችን በመውሰድ በአጠቃላይ በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ በማሳጣት ጉዳት በማድረስ መንግስታዊ ወይም ህዝባዊ የድርጅት ሰነዶችን አመሳስሎ ማዘጋጀትና ሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።

ተከሳሹ በዛሬው ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሰው የተደረገ ሲሆን ከጠበቃ ጋር ተማክሮ እንዲቀርብ ለነገ በይደር ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.