በመዲናዋ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ከ260 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ከ260 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በህብረተሠቡ ጥቆማ ተያዘ።
የአፈር ማዳበሪያው የተያዘው በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በተለምዶ ገደል ግቡ ጠጅ ቤት ተብሎ ከሚጠራው ከአንድ ግለሠብ መኖሪያ ግቢ ውስጥ በተሠራ የቆርቆሮ መጋዘን ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በህገ-ወጥ ተግባር የግል ጥቅማቸውን በማካበት ሰው ሰራሽ የሆነ የአፈር ማዳበሪያን እጥረት በመፍጠርና ዋጋው እንዲንር በማድረግ በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚሞክሩ አካላትን ከህገ-ወጥ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ፖሊስ አሳስቧል፡፡