Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የተሰረቁ ተንቀሳቃሽ ስልኮች በሕጋዊ ስም በተከፈቱ የንግድ ሱቆች ውስጥ ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ አካባቢዎች የተሰረቁ ተንቀሳቃሽ ስልኮች በሕጋዊ ስም በተከፈቱ የንግድ ሱቆች ውስጥ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ በሕጋዊ የሞባይል ስልክ እና የቴሌቪዥን ጥገና ሱቅ ሽፋን ከግለሰቦች የተሰረቁ ስልኮችን እየገዙ ሲሸጡ ከነበሩ ግለሰቦች ሱቅ ውስጥ በርካታ ተንቀሳቃሽ ስልኮች መያዛቸው ተገልጿል፡፡

ኤድናሞል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሞባይል ጥገና ስራ በሚሰሩ 4 የንግድ ሱቆች ላይ በፖሊስ በተከናወነ ብርበራ ነው ከተለያዩ ቦታዎች ተሰርቀው የተከማቹ ሞባይል ስልኮች የተዘያዙት፡፡

ከሞባይል ስልኮቹ በተጨማሪ የወንጀል ፍሬ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ እና በጥገና ቤቶቹ ውስጥ የተገኙ የተለያየ መጠን ያላቸው ስክሪን ቴሌቪዥኖች መያዛቸው ተጠቁሟል፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ አራት ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈፀመባቸው ወንጀል ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ቴሌቪዥን የተወሰደባቸው ግለሰቦች አንበሳ ጋራዥ ጀርባ በሚገኘው የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ እየቀረቡ ማረጋገጥ ይችላሉ ተብሏል፡፡

በወንጀል ምክንያት የተገኙ ንብረቶችን ከወንጀል ፈፃሚዎቹ በሚገዙ ግለሰቦች ላይ ተከታታይነት ያለው እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ችግሩ በዘላቂነት እስኪቀረፍ ድረስ በሕግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፖሊስ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.