ሐረር ከተማን ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐረር ከተማን ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡
የሐረሪ ብሄራዊ ጉባኤ 6ተኛ ዙር 2ኛ አመት 2ተኛ መደበኛ ጉባኤውን የተለያዩ ወሳኔዎች በማሳለፍ አጠናቋል።
አቶ ኦርዲን በድሪ በበጀት አመቱ ሐረር ከተማ ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች መታየታቸውን እና በበጀት አመቱ የሐረሪን ባህል፣ ቅርስና ታሪክን ከማጎልበት አኳያ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የሐረሪ ቋንቋን ከማጎልበትና ለማሳደግ በተደረገው ጥረት በቋንቋው የተማሩ ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ በዲግሪ መርሃግብር ማስመረቅ መቻሉን ገልጸዋል።
የክልሉ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ከመጠበቅ ባሻገር በሐረር ከተማ የሚገኙ 4 ሙዚየሞች እውቅና ማግኘታቸው የቱሪዝም ዘርፍን ያሳድገዋል ብለዋል።
በተጨማሪም የሐረሪ ባህላዊ የአለላ ስፌት ምርት አለም አቀፍ ብራንድ መሆኑ የክልሉን መልካም ገፅታ ከመገንባት ባለፈ የስራ እድል በመፍጠር አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።
የሐረር ከተማን የአለም አቀፍ የቅርስ ከተሞች አባል ከተማ ሆና መመዝገቧ ለሀገር ገፅታ ግንባታ ትልቅ ሚና እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።
ጁገልን ለነዋሪዎቿ ምቹና ለቱሪዝም ዘርፍ ሳቢ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የሸዋል ኢድ ክብረ በአል ባህሉንና ትውፊቱን በጠበቀ ሁኔታ በአንድነት በማክበር በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተደረጉ የሚገኙ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንስተዋል።
በጉባኤውም በበጀት አመቱ የተከናወኑ ተግባራትን አፈጻጸም እና የ2016 እቅድን በመገመገም በሙሉ ድምፅ በማጽደቅ ጉባኤውን አጠናቋል።