በቀደምት አርበኞች እግር እንደ መተካታችን እኛ የዚህ ትውልድ አባላትም የአንድነት፣ የሰላምና የብልጽግና ፋና ወጊዎች ነን- ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቀደምት አርበኞች እግር እንደ መተካታችን እኛ የዚህ ትውልድ አባላትም የአንድነት፣ የሰላምና የብልጽግና ፋና ወጊዎች ነን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ 79ኛው ዓመት የኢትዮጵያዊያን አርበኞች የድል በዓል አስመልክተው በፌስቡክ ገፃቸው መልእክት አስተላልፈዋል።
የመልእክታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ከዘመኑ ቀድሞ
ነግቶ የጨለመ፤
ጀግና ወድቋል ከፊት
እኛን እያለመ
ስለኛ እያሰበ።
ከሁሉም ነገር በላይ ሀገርና ሕዝብ አስቀድመው ለነጻነታችን ዋጋ የከፈሉትን አባት እና እናት ዐርበኞች ዛሬ እንዘክራለን።
ስለ ሀገራቸው እና ስለ ሕዝባቸው ሲሉ ተዋግተዋል። ለኢትዮጵያ የነበራቸው አቻ የለሽ ፍቅር በደም እና በሕይወት መሥዋዕትነት ተገልጧል። ይህንን ያደረጉት እንዲያው ለዝና ሳይሆን በአንድነት ለምትቆም ሉዓላዊት ሀገር ነው።
በቀደምት አርበኞች እግር እንደ መተካታችን፣ እኛ የዚህ ትውልድ አባላትም የአንድነት፣ የሰላም እና የብልጽግና ፋና ወጊዎች ነን። እናቶቻችን እና አባቶቻችን የወሰኑት ታሪካዊ ውሳኔ ነጻነት፣ ሀገርና ሉዓላዊ ሕዝብ ከምንም በላይ መሆናቸውን አሳይቶናል።
ከታሪካችን በመማር ተስፋ መቁረጥን ሳይሆን ዕድገትን፣ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን፣ኪሣራን ሳይሆን ትርፍን፣ ቀውስን ሳይሆን ብልጽግናን እናያለን፡
ክብር ለአርበኞቻችን!