በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለኮቪድ መከላከያ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለኮቪድ መከላከያ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ድጋፉ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም የኢፌዲሪ ሚሲዮኖች ኮቪድ 19 ለመከላከል የተደረገ መሆኑን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሰራተኞች ለወረርሽኙ መከላከል የ4 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውም ተገልጿል።
ድጋፉ በብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ስር የተቋቋመው የውጭ ድጋፍ አሰባሰቢ ንኡስ ኮሚቴ አስተባባሪነት መሰብሰቡም ነው የተገለጸው።
በዚህም በምስራቅ አውስትራሊያ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያደረገችውን የገንዘብ ድጋፍ በመወከል የማዕከላዊ እና የምዕራበ ጎንደር ሊቀ ዻዻስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ዮሀንስ፣ አገር ውስጥ የሚገኘው የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዱላዚዝ ኢብራሂም እንዲሁም የዩኤስ ኮሌጅ ባለቤት አቶ ቶላ ገዳ ተገኝተው ለንኡስ ኮሚቴው ድጋፋቸውን በቼክ አስረክበዋል።
ኮሚቴው ባለፉት ሳምንታት ከተለያዩ ሃገራት ሃብት የማሰባሰብ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
በተለያዩ የዓለም አገራት የተቋቋሙ 60 የኢፌዲሪ ሚሲዮኖች የኮሚቴውን እቅድ መነሻ በማድረግ በልዩ ልዩ ደረጃዎች ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙም ነው የተገልጸው።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙ ሚኒስትሮች በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጀች እና ዲፕሎማቶች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ለወገን እያደረጉ ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኮሮና ቫይረስ የደቀነውን ስጋት መቋቀም የሚቻለው ሁሉም አካል በሚችለው አቅሙ ሲረዳዳ እና ሲተባበር በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስትሮቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!