የጉምሩክ ኮሚሽን ከሩሲያ ጉምሩክ አስተዳደር ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከሩሲያ ጉምሩክ አስተዳደር ጋር የዋጋ ቅብብሎሽ ስርዓትን ማሳለጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የጎምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንደገለፁት÷ ከሩሲያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ኮሚሽኑ ከሩሲያ ጉምሩክ አስተዳደር ጋር የዕቃዎችን የዋጋ ቅብብሎሽ ማሳለጥ የሚችል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ይህ ስምምነት ከሩሲያ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እቃዎችን ትክክለኛ ዋጋ መረጃ ለማግኘት እና መንግስት ከገቢ እቃዎች ላይ ቀረጥ እና ታክስ በአግባቡ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም ስምምነቱ በገቢ እቃዎች ዙሪያ የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ከሩሲያ ጉምሩክ አስተዳደር ጋር በነበራቸው ውይይት በተጨማሪም የአደንዛዥ እፅ ዝውውርን እና ሀገር አቋራጭ የኮንትሮባንድ ዝውውርን ለመከላከል በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ