Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።

አዲሱ የባንኩ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ ሐምሌ 31 ቀን ጀምሮ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ባንኩ አስታውቋል።

በጉብኝታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ፥ ከገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ እና ከብሄራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈም ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር በባንኩ እና በአፍሪካ ህብረት መካከል አጋርነትንና ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩም ነው ባንኩ ያስታወቀው።

ለሴቶች እና ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ እድሎችን መለየት የጉብኝታቸው ዋነኛ ትኩረት ሲሆን፥ የጨርቃ ጨርቅ እና ጫማ ፋብሪካዎችን እንዲሁም ከአርሶ አደሮች ጋር በማስተሳሰር የሚካሄደውን የብቅል ማምረት ሂደትን እንደሚጎበኙም ታውቋል።

ከዚህ ባለፈም የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ከስራ አስፈጻሚዎች እና ከቢዝነስ መሪዎች ጋር ውይይት ያደርጋሉም ነው የተባለው።

አጃይ ባንጋ ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ የቀድሞውን የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስን በመተካት የባንኩ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።

አጃይ ባንጋ ከዚህ ቀደም በፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ከባለሙያነት እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት የሰሩ ሲሆን፥ ማስተር ካርድን ለ11 ዓመታት በውጤታማነት መምራታቸው ይነገራል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.