Fana: At a Speed of Life!

ሰዎች ለኮቪድ 19 ህክምና ፈዋሽነታቸውያልተረጋገጡ ባህላዊ መድሃኒቶችን መጠቀም የለባቸውም -የዓለም ጤና ድርጅት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም የጤና ድርጅት ሰዎች ለኮሮና ቫይረስ ሕክምና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ ባህላዊ መድኃኒቶችን እንዳይጠቀሙ አስጠነቀቀ።

ተቋሙ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው ሶስት የአፍሪካ ሀገራት ኮቪድ 19 በሽታን ያድናል የተባለውን ባህላዊ መድሀኒት ከማዳጋስካር እናስመጣለን ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በባህላዊ መድኃኒቶች እና እፅዋት ላይ የተመሠረተ ፈጠራን የሚያደንቅ ቢሆንም “ውጤታማነታቸው እና አሉታዊ የጎንዮሽ ጉዳታቸው መፈተሽ አለበት” ብሏል።

ምንም እንኳን መድሀኒቶቹ ከባህላዊ ሕክምናው የተገኙ ቢሆንም በትክክለኛ ሙከራዎች በኩል ያለፉ መሆን ይገባቸዋል ነው ያለው።

ከዚያም ባለፈ “አፍሪካውያን በሌሎች የዓለም ክፍል ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ መመዘኛዎችን ያለፈ መድሃኒት መጠቀም አለባቸው” ብሏል።

ባለፈው ሳምንት የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በቪድዮ ባደረጉት ስብሰባ በሀገራቸው ኮሮናን ያድናል ስላሉት ኮቪድ ኦርጋኒክ ስለተባለ ባህላዊ መድሀኒት መናገራቸው ተሰምቷል።

በዚህም የአፍሪካ ህብረት የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከያ ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) በምርቱ “ደህንነት እና ውጤታማነት” ላይ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ማየት እንደሚፈልግ ገልጿል ነው የተባለው።

በማዳጋስካር ኮቪድ-ኦርጋኒክ በመባል የሚታወቀው ይህ ባህላዊ መድሀኒት ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የማዳን አቅሙ ያልተረጋገጠ ከመሆኑም ባለፈ ከአለም አቀፉ የጤና ድርጅት የመድሀኒት አፈታተሽ መመሪያ ጋር የተጣጣመ አለመሆኑም ተነግሯል።

በዛሬው እለት የዓለም ሀገራት መሪዎች ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማግኘት ለሚደረገው ጥረት የሚውል ከ8 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማግኘት ከ12 እስከ 18 ወራት ወይም እስከ በፈረንጆቹ 2021 አጋማሽ ድረስ ሊወስድ ይችላል ብለው እንደሚያስቡ ዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ምንጭ፦ ቢ.ቢ.ሲ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.