Fana: At a Speed of Life!

800 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና ዩሪያ ወደ ትግራይ ክልል ገብቷል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2015 /2016 ምርት ዘመን 400 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 400 ሺህ ኩንታል ዩሪያ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ተገልጿል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርና እና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ዳይሬክተር ገብረስላሴ ኪዳነ እና የሕብረት ስራ ማህበራት ገበያ ልማት ኤጀንሲ ሃላፊ ነጋ አሰፋ ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ገብረስላሴ ኪዳነ በመግለጫቸው÷በትግራይ ክልል ለምርት ዘመኑ 400 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 400 ሺህ ኩንታል ዩሪያ ፍላጎት እንደነበር አንስተዋል፡፡

አሁን ላይም የተጠየቀው ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ወደ ክልሉ በመግባቱ አርሶ አደሩ ሲያነሳው የነበረው ጥያቄ መመለሱን ተናግረዋል፡፡

ወደ ክልሉ ከገባው ማዳበሪያ ውስጥም ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ወደ ወረዳዎች መሰራጨቱን ነው የገለጹት፡፡

አቶ ነጋ አሰፋ በበኩላቸው÷ ማዳበሪያው ወደ አርሶ አደሩ የሚሰራጨው በመንግስት አማካይነት ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በዩኒየኖች እና ሕብረት ስራ ማህበራት የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዝቅተኛ መሸጫ ዋጋ 3 ሺህ 600 ብር ሲሆን÷ ከፍተኛው ደግሞ 5 ሺህ 800 ብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ውጪ ሲሸጥ የተገኘ ግለሰብ በሕግ እንደሚጠየቅ ገልጸው÷አርሶ አደሩም ህገ ወጦችን ሲመለከት ለጸጥታ አካላት እንዲያሳውቅ ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.