Fana: At a Speed of Life!

ውሺ የቻይና የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማስፋት እየሰራሁ ነው አለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ አስተዳደር ውሺ የተባለው የቻይና የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ የልብስ እና የግብርና ምርቶች በማቀነባበር የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማስፋት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ኩባንያው በአስተዳደሩ ነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈና በ220 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተገነባ ነው፡፡

ፋብሪካው በጨርቃ ጨርቅ፣ በጥጥ ፋብሪካና በግብርና ምርቶች ላይ በመሰማራት የኢንቨስትመንት ዘርፉን በመደገፍ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ ተነስቷል፡፡

ድሬዳዋን የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እና የቱሪዝም ማዕከል በማድረግ በራዕይ ደረጃ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የነጻ የንግድ ቀጠና፣ ደረቅ ወደብ እንዲሁም የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር መጀመርን ማብሰራቸው ይታወሳል፡፡

በዚህም በአስተዳደሩ የኢንዱስትሪና የንግድ እንቅስቃሴ በፍጥነት ማደጉን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሀርቢ ቡህ ገልጸዋል፡፡

ከኩባንያው ባለቤትና ስራ አስኪያጆች ጋር በግብርና በሌሎች ምርቶችን በማስፋት በኩል ዘርፉን በመደገፍ ረገድ በአስተዳደሩ ባሉ ምቹ መደላደሎች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው አክለውም ፥ ቢሮው ኢንዱስትሪውን በመደገፍ በርካታ እንቅስቃሴዎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በአስተዳደሩ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት የሚመጡ ባለሃብቶችን በማበረታታት በቂ መሬት፣ የሰው ኃይል፣ መሰረተ ልማት፣ ብድርና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያገኙ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡

በዚህም በተገባደደው ዓመትም 34 ነጥብ1 ቢሊየን ያስመዘገቡ 214 ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማሰማራት ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

እስካሁንም በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ 458 ፋብሪካዎች ወደ ማምረት መግባታቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.