የሐይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ እና ከጅስራ ኮንሶርቲዬም ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ”የሐይማኖት አስተምህሮ ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት አካሂዷል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በወቅቱ እንዳሉት÷ ሁሉም ሃይማኖቶች የቆሙበት መሠረት ሰላም፣ ዕርቅና ይቅርባይነት ቢሆኑም በሀገራችን ሐይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግጭቶች ለሰላም መደፍረስ እንደ አንድ ምክንያት ሆነዋል።
የችግሩ መነሻ ምክንያቶች የሐይማኖት ተቋማት በውስጣቸው የሚነሱ ችግሮች እና በሐይማኖቶች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
ሚኒስቴሩ በሐይማኖቶች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር እና የሐይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ ላይ ሚናቸው እንዲወጡ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የውይይቱ ዓላማ ሐይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚከሰቱ ችግሮችን በሰከነ መንገድ ተወያይቶ ለመፍታት ያለመ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡