የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን የሚገኘውን የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ፡፡
የዞኑ ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ዮሴፍ ማሩ (ዶ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ የጌዴኦ መልክዓ ምድርን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የዞኑ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡
በዩኔስኮ ከሚመዘገቡት ውስጥ የጌዴኦ ማህበረሰብ የመሬት አያያዝ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው÷ በስሩ ጥንታዊ የስልጣኔ አሻራ የሆኑት ታሪካዊ ቅርሶች፣ ትክል ድንጋይ፣ የዋሻ ላይ ጽሑፍ እንዲሁም በባህላዊ መንገድ ብቻ የሚተዳደሩ ደኖች ይገኙበታል ብለዋል፡፡
በማስመዝገብ ሂደቱ የሀገር ውስጥም የውጭም ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን በመጥቀስ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ሰነዶችም መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት፡፡
በዞኑ በምስራቅ አፍሪካ ረዥም እድሜ አስቆጥረዋል የተባሉ 10 ሺህ የሚደርሱ የትክል ድንጋዮች እንዳሉና እነዚህም በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ በዕጩነት የቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ቅርሶች ሲመዘገቡ ለሀገር የሚሰጡት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም ከፍተኛ ነው ያሉት ሀላፊው÷መልክዓ ምድሩን የማስመዝገብ ሂደት እንደተጠናቀቀም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ከጳጉሜን 5 ቀን እስከ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ሪያድ ላይ በሚደረገው 45ኛው የዩኔስኮ ኮንፈረንስ ላይ ባህላዊ መልክዓ ምድሩ ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ቅርሶችን ማስመዝገብ ብቻ በቂ አለመሆኑን በመጥቀስ የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድር በተገቢው ለምቶ ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ሀብቱ በተገቢው መንገድ ሊጠበቅ ይገባልም ነው ያሉት።
በየሻምበል ምሕረት