የአፍሪካ ቱሪዝም ሚኒስትሮች ለዘላቂ ቱሪዝም ልማት እንዲሰሩ ጋና ጥሪ አቀረበች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ቱሪዝም ሚኒስትሮች ለአህጉሩ ዘላቂ ቱሪዝም ልማት እንዲሰሩ የጋና ቱሪዝም፣ ኪነ-ጥበብና ባህል ሚኒስትር ኢብራሂም መሀመድ አዋል (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአፍሪካ ቱሪዝም ሚኒስትሮች አካባቢን ለመጠበቅ እና ማህበረሰቡ ከቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ዘላቂ የቱሪዝም ሥርዓቶችን መከተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሚኒስትሩ ጥሪውን ያስተላለፉት ባለፈው ሐሙስ በሞሪሺየስ በተካሄደ ጉባኤ ለተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ጋና በተመረጠችበት ወቅት ነው፡፡
የጋና ፕሬዚዳንት ናና አዶ ዳንኩዋ አኩፎ-አዶ ቱሪዝም፣ ኪነ-ጥበብና ባህል ለአገራዊ ልማት ውጤታማ የሆነ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቅርቡ ኃላፊነት መስጠታቸውን የኦል አፍሪካ መረጃ ያመላክታል።
በፈረንጆቹ 2025 የጋና ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ በመሆን ወደ ሁለት ሚሊየን ጎብኚዎችን እንድታስተናግድና ከዚህም በዓመት 6 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት እንዲሰራ አቅጣጫ መሰጠቱን ዘገባው አክሎ ገልጿል።
የጋና የጉዞ እና ቱሪዝም እድገት በዓለምአቀፍ ጉባኤ በተምሳሌትነት አጀንዳ እንዲሆን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ቃል የገቡት ሚኒስትሩ፤ የአህጉሪቱን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በቱሪዝም መሠረተ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በቱሪዝም የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የተዋናዮችን አቅም ማጎልበት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ናሚቢያ፣ ታንዛኒያ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሌሎች ለዓለም ቱሪዝም ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት የተመረጡ አገራት መሆናቸው ተጠቁሟል።
የአዳዲሶቹ አባላት ምርጫም በጥቅምት ወር በኡዝቤኪስታን በሚካሄደው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በይፋ እንደሚፀድቅ ተመላክቷል።