Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ቱርክን በተለያዩ ዘርፎች በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ቱርክን በንግድ፣ በጤና፣ በኢንቨስትመንት፣ በባህል እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ቆሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር በርክ ባራን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች በንግድ፣ በጤና፣ በኢንቨስትመንት፣ በባህል እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ዲማ (ዶ/ር) አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በመፍጠር አካባቢያዊ ሰላም እንዲረጋገጥ ጠንክራ እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ለረጅም ዓመታት የቀጠለው የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ብሔራዊ ጥቅም መሰረት ያደረገ ወዳጅነት እንደሆነም ገልፀዋል።

የቱርክ አምባሳደር በርክ ባራን በበኩላቸው÷ የቱርክ ባለሀብቶችና ምሁራን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በትምህርት፣ በጤና እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ በስፋት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በቀጣይም ግንኙነቱን በተሻለ ሁኔታ ለማጠናከር በሁለቱ ሀገራት መካከል የሕዝብ ለሕዝብ እና የፓርላማ ዲፕሎማሲ ስራዎች እንደሚሰሩ አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

የዜጎችን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያረጋግጡ ስራዎችን ለማስቀጠል ሰላም ወሳኙን ሚና ይጫወታል ያሉት አምባሳደሩ÷ቱርክ  ለኢትዮጵያ ሰላም እና እድገት ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች ማለታቸውን ከህዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.