Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኮሮና ቫይረስ ምላሽ ሰጭ ግብረ ሃይል እንደሚበተን አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚየ 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኋይት ሃውስ ስር የተቋቋመው የኮሮና ቫይረስ ምላሽ ሰጭ ግብረ ሃይል እንደሚበተን አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ አሪዞና የሚገኝ የአፍ መሸፈኛ ጭምብል ማምረቻ ፋብሪካን በጎበኙበት ወቅት “ሃገራችንን ወደ ነበረችበት እንመልሳታለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

በወቅቱ ግብረ ሃይሉን የሚመሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ማይክ ፔንስና ግብረ ሃይሉ ጥሩ ስራ መስራታቸውን ያነሱት ትራምፕ፥ ከዚህ በኋላ “ደህንነት እና መደበኛ እንቅስቃሴን መሰረት ያደረገ” የተለየ አካሄድ እንደሚኖር ጠቅሰዋል።

የተለየ ያሉትን አካሄድ የሚመራም አዲስ ቡድን ሊቋቋም እንደሚችልም ነው ትራምፕ የተናገሩት።

ትራምፕ በወቅቱ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ግባቸውን አሳክተው እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄም “ገና ነን” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ማይክ ፔንስ በበኩላቸው አወዛጋቢ ለተባለው የትራምፕ ሃሳብ ተፈጻሚነት ማረጋገጫ ሰጥተዋል ነው የተባለው።

እንደ ፔንስ ገለጻ የትራምፕ ሃሳብ ምናልባትም በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተፈጻሚ ይሆናል።

አሁን ላይ በአሜሪካ በቫይረሱ ሳቢያ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ72 ሺህ በላይ ሲሆን፥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

ከዚህ ባለፈም በየቀኑ በቫይረሱ አዳዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ20 ሺህ በላይ ሲሆን፥ የሞት መጠኑም ከ1 ሺህ በላይ ሆኗል።

አሜሪካና ህዝቦቿ የተጋፈጡትን ይህን ከባድ ፈተና ለመቀነስና ለመከላከል የተቋቋመውን ግብረ ሃይል ትራምፕ እንደሚበተን ያነሱት ሃሳብ ግን ከበርካቶች ተቃውሞና ትችት እያስተናገደ ነው።

የሃገሪቱ የጤና ባለስልጣናትና ባለሙያዎችም ሀገሪቱ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ በተመለሰችበት ቅጽበት የቫይረሱ ስርጭት ይበልጥ ይጨምራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እንደ ባለስልጣናቱ የትራምፕ መደበኛ እንስቅቃሴን በቅርቡ ተግባራዊ የማድረግ እቅድ እውን የሚሆን ከሆነ አሜሪካ ለቀጣይ ዙር ከባድ ፈተና መዘጋጀት ይጠበቅባታል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.