በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ከ2 ሚሊየን በላይ አርብቶ አደር ተጠቃሚ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ከ2 ሚሊየን በላይ አርብቶ አደር ተጠቃሚ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱንም ሚኒስቴሩ የገለጸ ሲሆን÷ፕሮጀክቱ ለስድስት አመት የሚቆይ ነው ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታም እንዳሻሻለ ተጠቅሷል፡፡
ሚኒስቴሩ የ2015 ዓ.ም አፈፃፀምና የ2016 እቅድን በተመለከተ ግምገማ እያካሄደ ሲሆን÷በበጀት አመቱ ከ2 ሚሊየን በላይ አርብቶ አደር የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማት አስተዳደር የአርብቶ አደሩ የኑሮ ማሻሻያ መሰረታዊ አገልግሎት ማስፋፋትና አቅም ግንባታ ዘርፍ የፕሮጀክት ማኔጅመንት እና ክትትል የሚሉ ዘርፎችን በመለየት እየተሰራም መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ሶማሌ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ደቡብ ፕሮጀክቱ እየተተገበረ ያለባቸው ክልሎች ሲሆኑ÷ አጠቃላይ 100 ወረዳዎችን ያካተተ ነው፡፡
በ2016 በጀት አመትም 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልገው ሚኒስቴሩ የገለጸ ሲሆን÷ በዓለም ባንክ እና በዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ፕሮጀክቱ እንደሚደገፍም ተጠቁሟል፡፡
የፕሮጀክቱ የትኩረት መስክ- በአርብቶና በከፊል አርሶ አደሩ አካባቢዎች የተቀናጀ ልማት ማፋጠን፣ የእንሰሳት እርባታን ማሻሻልና ገበያ ማስፋፋት፣ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችን ማዘመንና የሰው ሃይልን ማብቃት ነው ተብሏል።
በፈቲያ አብደላ