በመዲናዋ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ682 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው የ2015 ዓ/ም በጀት ዓመት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ682 ነጥበ 5 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምሥክር ነጋሽ በ2015 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከ682 ነጥበ 5 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
ገንዘቡ የተሰበሰበው በቦንድ ግዢና በስጦታ መሆኑን ገልጸው በበጀት ዓመቱ በእቅድ ከተያዘው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር 99 ነጥብ 6 በመቶ አፈጻጸም እንዳለው ነው ያመላከቱት።
730 የህዝብ መድረኮችና የጎዳና ላይ ንቅናቄዎችን በማዘጋጀት ገንዘቡ ሊሰበሰብ መቻሉም ነው የተገለጸው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ባለኃብቶች ባለፉት 12 ዓመታት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚውል ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
በህዝብ ንቅናቄና ተሳትፎ ከ10 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በንቅናቄ፣ በመድረክና በጉብኝት ተሳትፈዋል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡