Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጎብኚዎች ለመሳብ የተከናወኑ ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከውጭ  ሀገራት ጎብኚዎች የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተከናወኑ ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አለማየሁ ጌታቸው እንደገለጹት÷ በበጀት ዓመቱ የውጭ ቱሪስቶችን በመሳብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት ተሰርቷል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ግኝትና የስራ ዕድሎችን በማስፋፋት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መሰራቱንም አንስተዋል፡፡

የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች መዳረሻ የሚሆኑ የቱሪዝም ቦታዎችን የማስተዋወቅ እና መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ስራ መከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ለቱሪዝም ልማት 132  ነጥብ 1 ሚሊየን ብር መደበኛ እና 401 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የካፒታል በጀት ተመድቦለት እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡

በዓመቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብ ታቅዶ 969 ሺህ በላይ ቱሪስቶች በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንደጎበኙ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ከተለያዩ የቱሪዝም አገልግሎቶች 3 ነጥብ 63 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ነው አቶ አለማየሁ የገለጹት፡፡

በቀጣይም ተደራሽ የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን በመጠቀም የውጭ ጎብኚዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

 

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.