ራሱን ደብቆ ታግቻለሁ በማለት ከቤተሰቡ 120 ሺህ ብር ሊቀበል የነበረው ወጣት በቁጥጥር ስር ዋለ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለተከታታይ ሶስት ቀናት ራሱን ደብቆ ታግቻለሁ በማለት ከቤተሰብ ገንዘብ ሲጠይቅ የነበረው ወጣት በቁጥጥር ስር ዋለ።
ነዋሪነቱ በታች አርማጭሆ ወረዳ ዶጋው ቀበሌ የሆነው የ18 ዓመት ወጣት ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሳንጃ ከተማ ከአክስቱ ልጅ ቤት በመሸሸግ ታግቻለው በማለት ከ120-150 ሺህ ብር ቤተሰቦቹን መጠየቁን የታች አርማጭሆ ወረዳ የሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በዚህም በድርድር ከአክስቱ ልጅ ጋር በመሆን 120 ሺህ ብር ለመቀበል ሲሞክሩ ከህብረተሰብ በደረሰ ጥቆማ በሳንጃ01 ቀበሌ የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አንተነህ ታደሰ ተናግረዋል ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል በተደረገው እንቅስቃሴ ታግቻለው በማለት ቤተሰቦቻቸውን ከ90 ሺህ እስከ 400 ሺህ ብር ሲጠይቁ የነበሩ 6 ግለሰቦች እንደነበሩ ኃላፊው መጠቆማቸውን ከወረዳው ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።